መሪዎች ሳይሆኑ ክስተቶች ናቸው። 

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ እና የፕሬዚደንት ለማ የአሜርካ ጉብኝት የተሳካ ነበር ማለት ብቻ አይገልፀውም። መንትያ መሪዎቹ ዲያስፖራውን ደረማመሱት ብቻም አይበቃም። ዲያስፖራውን አስታርቀው፣ ግርግዳውን ንደው፣ ድልድይ ሰርተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱም ያንሳል።

የሆነው ነገር አስገራሚ ነው። ለማና አብይ ተይቶም፣ ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ዲያስፖራውን በፍቅር እጅ አሰጥተው፣ የዲያስፖራውን የፓላቲካ፣የሃይማኖትና የኮሚኒቲ መሪዎች እና ተቋማቱን ወስደው፣ ራሳቸውን የዲያስፖራው የፓላቲካ፣ የኢኮኖሚ፣የሃይማኖት እና የኮሚኒቲ መሪዎች አድርገው ነው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት።

በአራት ነጥቦች ሳጠቃልለው ለማና አብይ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት፣

1 ኛ፣ በውጭ እና በአገር ውስጥ ለሁለት ተከፍላ ከ27 ዓመት በላይ ሲናቆሩ የቆዩትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ አስታርቀው፣አንድ አድርገው፣ መሪዎቹን ጭነው፣ ራሳቸውን የሁሉ መሪና በፕትሪያርክ አድርገው ነው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት። ዝርዝሩን በውል ያላወኩት በኢትዮጵያ ሙስሊም መሪዎች መካከል የነበረውን ልዩነት ገፋው ወዳጄ ሼህ ከሊድን ጭምር ወስደው ነው የሄዱት። በኢትዮጵያ የሃይማኖቶች አንድነትን አረጋግጠው ተመልሰዋል። ለ27 ዓመት እዚህን ለማስታረቅ የባከነው ጉልበት፣ገንዘብ እና ጊዜ በአብይና ለማ የአራት ቀን ጉብኝት ምላሽ ሲያገኝ በማየት እግዚአብሄርን ከማመስገን ውጭ ብዙ ቋንቋ የለውም። ተአምር ነው።

2ኛ፣ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ በስደት ይዳክሩ ለነበሩት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ተሰብስበው፣ ድልድይ ሰርተው፣ መሪ ሆነው፣ ከ50 ዓመት በላይ በስደት የቆየውን የኢትዮጵያ ፓላቲካ በስደት ከቆየበት ከአሜርካ ጠራርገው ወስደው ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። በዚህ ጉብኝት በስደት ይኖር የነበረው የኢትዮጵያ ፓላቲካ እና ፓላቲከኛ (የኦሮሞን ጨምሮ) ኢትዮጵያ ተመልሷል። መሪዎቹም አብይ እና ለማ ናቸው።

3 ኛ፣ በተለይ በሜኔሶታ በተደረገው ስብሰባ እንደታየው ለማና አብይ ፓላቲካውን መቀማት ብቻ ሳይሆን የኦነግን ባንዲራ ጭምር ቀምተው፣ የኦነግ መሪዎች ሆነው፣ የኦሮሞን ፓላቲካ ከነባንዲራው ጠቅልለው ወስደው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ይህ ምናልባት ብዙዎች ያላስተዋሉት ትልቅ ተአምር ነው። ከዚህ በኋላ ለማ እና አብይ ተቀናቃኝ ያሌላቸው የኦሮሞ ፓላቲካ መሪዎች ናቸው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያንም ሆነ ምስራቅ አፍርካን ለመምራት ትልቅ ምሰሶ ይሆናቸዋል። ( በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ዋሽንግተን ዲሲ እና ኤል ኤን ብቻ እንዲጎበኙ የተነደፈው እቅድ ተቀይሮ ከዲሲና ኤል ኤ በተጫማሪ በፓላቲካ ኃይል አሰላለፍም ሆነ በዲሞግራፊ ከዲሲ እና ኤል ኤ የሚትለየውን ሜኔሶታን እንዲጎበኙ ተደጋጋሚ ሃሳብ ለኢትዮጵያ ኤምባሲም ሆነ በአሜርካ በሚገኙ የኦሮሞ ኮሚዩኒቲ ድርጅቶች ቴሌ ኮንፍረንሶች ላይ እና ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለመጣው የአብይ ኮሚቴ መሪ ዲሲን ሲጎበኙ ሃሳብ ያቀረብነው እኔ እና ብርሃኔ ቤካ ገለቶ ነን። ስለዚህ በሜኔሶታው ጉብኝት ስኬት ልዩ ደስታ ይሰማናል። በዲሲው ሁኔታ ምክንያት እኔም ሆንኩኝ ብርሃኔ ሜኔሶታ ሄደን የደስታው ተካፋይ ባለመሆናችን ቅር ተሰኝተናል።)

4ኛ፣ ጉብኝቱ በዲያስፖራ ያሉትን አክቲቪስቶች፣ የፓላቲካ መሪዎች እና ሙሁራን ሁሉ እጅ አሰጥቷል። አሁን የአብይና የለማን አመራር ተቀብለን የለማን አገር ወደ ምንገነባበት የአገር ግንባታ ዘመን ተሸጋግረናል።

እኔም ኢትዮጵያን ወክዬ ወደምሰራበት ወደ ዲፕሎማሲው ዓለም ወይም ወደ ፓሊሲ ስራዬ ለመመለስ ወስኛለሁ። ሁላችንም በአንድነት ኢትዮጵያን ትልቅ፣ የበለፀገች እና የሁላችንም የሚትሆን ገናና አገር አድርገን እንገነባታለን። ሁላችንም እነዚህን መሪዎች ሳይሆኑ ክስተቶች እግዚአብሄር ስለሰጠን እኳን ደስ አለን።