Tsegaye Ararssa: አዲስ ትርክት ለአዲስ አገር! (አልያ ዝም በሉ!)

አዲስ ትርክት ለአዲስ አገር! (አልያ ዝም በሉ!)
የሃበሻ ብሔርተኛነት በሆነ (ጠባብና ‘ፌክ’) የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያን መምራት አይቻልም። የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ያንድ መንደር ብሔርተኝነት ነው። አሁን አሁን ደግሞ ይሄ ‘ፌክ’ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት፣ ትግራይን እንኳን ማቀፍ እንደማይችል ግልፅ ሆኗል።

አብይ አህመድም እየተወነ ያለው (perform እያደረገ ያለው) ከዚሁ ፌክ ኢትዮጵያዊነት እስክሪፕት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ ነን ባይ ልሂቃን፣ ከመንደራቸው ውጪ ያለውን ኢትዮጵያዊ የሚያቅፍና እሴቶቻቸውንም በአግባቡ የሚገልፅ አገራዊ ብሔርተኝነት ለማሰብ፥ ለማለም፥ ለመቅረፅና ለመተግበር እንደማይችሉ በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል። የያዙት የፌክ ኢትዮጵያዊነት እስክሪፕት ተቀባይነት ያለው የአገር ማስተዳደሪያ ትርክት መሆን እንዳቃተው በገሃድ ተረጋግጧል። በ1966 ዓም በገሃድ፣ ትዕይንታዊ በሆነ ሁኔታ (spectacularly) መውደቁና መፈረካከሱ ቢታይም የደርግ መልሶ ጥገና (የ’ኢትዮጵያ ትቅደም’ ትርክት) እንኳን እንዲአገግም አላስቻለውም። የኢሕአዴግ የ’ከፋፍለህና አልጣተህ ግዛ’ (ያለዴሞክራሲ የሆነ ፌደራሊዝም) እስትራቴጂም ከጅምሩ አንስቶ ውሱንነቱ እየታየ ቢቆይም፣ ይኸው በቅርቡ እንደታየው በቄሮ ትግል በገሃድ እና ትዕይንታዊ በሆነ ሁኔታ ፍርስርሱ ወጥቶአል።

ደግሜ ደጋግሜ እላለሁ፦በእኩል ባለቤትነት፥ በእኩል መስራችነት፥ በእኩል አዕማድነት ላይ ያልተመሰረተ አገራዊ ማንነትና ብሔርተኝነት መጨረሻው መበታተንና ከባሰም እርስ በእርስ መተላለቅ ነው።

ለማ መገርሳ፣ በብአዴን ረዳትነት ሕወኅትን ከሥልጣን ማማ ለመግፋት ሲል የተጠቀመበትና ከወደቀበት ያነሳው የፌክ ኢትዮጵያዊነት ትርክት (‘ሱሴ ሱሴ’ የሚለው ዘፈን ማለት ነው!) ብአዴንን ከጎኑ ለማሰለፍ እንደ መታገያ ስልት (tactic) የተወሰደ ነበር። እንደ ስልት ጠቃሚ ሆኖ አልፏል። (ስልቱን ወደ መርህ የመቀየር ሙከራ ሲጀመር፣ ያ፣ በወቅቱ ‘የለማ መገርሳ ቅፅበት’ (The Lemma Megerssa Moment) ብዬ የገለፅኩት ወቅትም አብሮት ከስሟል።

አብይ አህመድ ጋ ሲደርስ ይሄ በስልትነት የተቀየሰ ትርክት፣ የመንግሥት ቀኖና (state orthodoxy) ሆኖ መጣ። በሥነ-ፅሁፋዊና መንፈሳዊ ቋንቋ (ይቅርታ፥ ፍቅር፥ ወዘተ) ታጅሎ፣ በማነቃቂያ የንግግር ስልት (motivational style) ቢቀርብም፣ አሁንም በይዘቱ፣ ያው ከአንድ መንደር ውጪ ተሰሚነት የሌለው፣ ያ ያረጀ ያፈጀ ‘ፌክ’ ኢትዮጵያዊነት ነው።

ይዘቱን አብራሩ ሲባሉ ከሚንተባተቡ አንዳንድ ምስኪን ካድሬዎቻቸውና ወዶ-ገብ አሸርጋጆች (unsolicited apologists) በቀር “የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ባላደራ ነን” የሚሉት ልሂቃን ያው የድሮውን እስክሪፕት ይዘው በድሮ መፈክር ከመፎከር፣ በድሮ ባንዲራ ከመጓተት፥ በድሮ ዜማ ከመዘመር ውጪ የሰጡት ትንተና እስካሁን የለም።

ይሄ ደግሞ ለአዲስ ዘመን፥ ለአዲስ አገር የሚሆን ትርክትም ሆነ ገዢ ሃሳብ እንደሌላቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

ያንን የሞተ ትርክት ከወደቀበት አንስቶ መድገምና መደጋገም፣ ለአገሪቱ ችግር መፍትሄ አይሆንም። ለራሳቸውም አይጠቅማቸውም።

ለአብይምቢሆን የማይመጥነው፥ ጠባብና የማይወጣው ቅርቃር ውስጥ አስገብቶ፣ በመጨረሻም፣ በዚህ በሞተ ትርክት ታጅሎ እንዲሞት ከማድረግ ውጪ አንዳች የሚፈይደው ነገር የለም።

ቢችሉ፣ ለአዲስ አገርና አገረ-መንግሥት የሚሆን አዲስ መሠረት መጣል መልካም ነው። ካልቻሉ፣ በድሮ ትርክት አገሪቱን ወደ ባሰ ጭለማ ለመውሰድ ወደኋላ መጎተቱን ይተዉ።

የቀድሞው ተረት አመንጪ፥ ወራሽና ተጠቃሚ እንደመሆናቸው፣ ከዚያ ተረት ውጭ ማሰብ አለመቻላቸው የሚጠበቅ ነው። አገሪቱን እንደመንደራቸው ብቻ በማየት ለመንደራቸው ማስተዳደሪያ እንኳን የማይመጥነውን ትርክት በሌላው ህዝብና በአገር ላይ የአገዛዝ ትርክት አድርጎ ለመጫን መሯሯጥ ግን ትክክል አይደለም፣ ሊፈቀድም አይገባም።

ይልቅ፣ ለእነሱም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚያዋጣው፣ የአገሪቷን ባለብዙ መሠረት (multi-foundational መሆኗን)፥ ባለ ብዙ አእማድ (multiple pillars ያላት መሆኗን)፥ ባለ ብዙ ብሔር (multinational)፥ ባለብዙ እምነቶች (multiconfessional)፥ ባለ ብዙ ቋንቋ (multilingual)፥ እና ባለብዙ ባህል (multicultural) መሆን ተረድቶ (ተቀብሎ)፣ ያለምንም ማመንታት ለዚህ የሚመጥን የአመራር ትርክት ማመንጨት፣ የሕግና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መዘርጋት (ወይም ያለውን በደንብ ፈትሾ ማቃናትና ማስተካከል)፣ እና የአስተዳደር ፥ የመብትና የተጠያቂነት ተቋማትን ማደራጀት ነው።

ከዚህ ውጭ ያለው ይዘት-የለሽ ‘የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት’ ለአገር የማይመጥን የመንደር ብሔርተኝነት ነው። ጫጫታውም ያው የተለመደው እኝኝና እዬዬ ነው።